በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ነፃ ፕሬስ ሰብዓዊ መብት ነው - አማንዳ ቤኔት


ነፃ ፕሬስ ሰብዓዊ መብት ነው - አማንዳ ቤኔት
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:02 0:00

ነፃ ፕሬስ ሰብዓዊ መብት ነው - አማንዳ ቤኔት

የአሜሪካ ድምፅ (ቪኦኤ) እናት ድርጅት በሆነው የዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ ሚዲያ ኤጀንሲ (ዩ.ኤስ.ኤ.ጂ.ኤም.) ሥር የሚሠሩ ጋዜጠኞች በአንዳንድ አፈና ባለባቸው ሁኔታዎች ውስጥ በየዕለቱ የፕሬስ ነፃነትን እየተከላከሉ መሆናቸውንና ለዚህም ምሥጋናቸውን ማቅረብ እንደሚሹ የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አማንዳ ቤኔት ዛሬ፤ ዓርብ ሚያዚያ 25 በመከበር ላይ ያለውን የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት አስታውቀዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት በዓለም ዙሪያ የፕሬስ ነፃነት ከባድ ፈተና ውስጥ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቤኔት ከዩኤስኤጂኤም እህትማማች የሚዲያ ተቋማት አንዱ የሆነውን የራዲዮ ነፃ አውሮፓ ወይም ራዲዮ ሊበርቲ ባልደረባዋን አልሱ ኩርማሼቫን አስታውሰው አልሱ ለወራት ያለአግባብ ተይዛ በምትገኝበት የሩሲያ እሥር ቤት ውስጥ በከበደ መጥፎ ሁኔታ ውስጥ ተይዛለች ብለዋል።

“ጋዜጠኛነት ወንጀል አይደለም፤ አልሱ ወደ ቤቷ መመለስ አለባት” ብለዋል ቤኔት።

በመረጃ ላይ የተመሠረተ ነፃና ገለልተኛ ዘገባ ማግኘት መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ አስታውሰው በሚያሳዝን ሁኔታ ግን በብዙ ቦታዎች የዩኤስኤጂኤም ባልደረቦችን ጨምሮ ጋዜጠኞች ሥራቸውን ስላከናወኑ ብቻ ዒላማ እንደሚደረጉ፣ እንደሚታሠሩና የከፋም እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል።

“በዓለም ዙሪያ የፕሬስ ነፃነት ፈተና ላይ ነው፤ ልንጠብቀው መፋለም አለብን። እናም ዛሬ፤ ባልደረቦቼ፤ ከእናንተ ጋራ እንዲሁም በራሳችን ተቋማት ውስጥም፣ በዓለም ዙሪያ ካሉም እጅግ የበረቱ ፈተናዎችን ተቋቁመው እውነትን በድፍረት ከሚዘግቡ ጀግናና ብርቱ ጋዜጠኞች ጋር በኅብረት እቆማለሁ“ ብለዋል አማንዳ ቤኔት።

ለቪኦኤ እያንዳንዱ ቀን የፕሬስ ነፃነት ቀን ነው”

ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቤኔት አክለውም “የእናንተ ዘገባዎች ለብዙዎች የተለየ የሕይወት መንገድ መኖሩን ማሳያ ነው“ ብለዋል። “እናንተ አማራጮች ወይም ምርጫ እንዳላቸው፣ ያሻቸውን የመልበስ፣ የፈለጉትን የማድረግ፣ የፈቀዱትን የማፍቀር ነፃነት እንዳላቸው ታሳያችኋላችሁ” ብለዋል።

የአሜሪካ ድምፅ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጃን ሊፕማን ባስተላለፉት መልዕክት “ለቪኦኤ እያንዳንዱ ቀን የፕሬስ ነፃነት ቀን ነው” ብለዋል።

“ከ1942 ዓ.ም. [በአውሮፓአቆጣጠር /በኢትዮጵያ ከ1934 ዓ.ም.] አንስቶ የቪኦኤ ጋዜጠኞች ነፃ ፕሬስ ዋጋ እንዳለው አሳይተዋል” ሲሉ አክለዋል ሊፕማን።

ቪኦኤ በየሣምንቱ በዓለም ዙሪያ ከ354 ሚሊዮን በላይ አድማጮችና ተመልካቾችን በ48 ቋንቋዎች እንደሚደርስ ሊፕማን አመልክተዋል። [ቪኦኤ] “የአሜሪካ ታሪኮችን ፕሬስ ነፃ ባልሆነባቸው ሃገሮች ውስጥ ላሉ ተመልካቾችና አድማጮች ያደርሳል” ብለዋል ሊፕማን።

“ሜይ 3 [ሚያዚያ 25] ጋዜጠኞች፣ በተለይ የቪኦኤና የዩኤስኤጂኤም ቤተሰቦች የፕሬስ ነፃነት በዓለም ዙሪያ እንዲፀና እየፈፀሙ ስላሉት ቁርጠኛነት እናደንቃቸው ዘንድ ከዓለም ጋር አብረን እንቆማለን”ብለዋል ሊፕማን።

የዛሬውን የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ለማክበር የዩኤስኤጂኤም እህትማማች ተቋማት፤ የነፃ እሥያ ራዲዮ፣ የነፃ አውሮፓ ራዲዮ ወይም ራዲዮ ሊበርቲ፣ የኩባ ብሮድካስቲንግ ቢሮ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ብሮድካስቲንግ መረብ እና የኦፕን ቴክኖሎጂ ፈንድ መሪዎችም መልዕክቶቻቸውን አስተላልፈዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG