በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዓለም ዙሪያ ሙስሊሞች የጋዛው ሰቆቃ ያጠላበትን የኢድ አልፈጥር በዓል አክብረዋል


ቱርክ፣ ኢስታንቡል በሚገኘው ታሪካዊው ሱልጣን አህመድ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው ኻያ ሶፊያ መስጊድ ውጪ ሙስሊሞች የኢድ አልፈጥር የመጀመሪያ ቀን ፀሎት ሲያካሂዱ - ሚያዚያ 10፣2024
ቱርክ፣ ኢስታንቡል በሚገኘው ታሪካዊው ሱልጣን አህመድ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው ኻያ ሶፊያ መስጊድ ውጪ ሙስሊሞች የኢድ አልፈጥር የመጀመሪያ ቀን ፀሎት ሲያካሂዱ - ሚያዚያ 10፣2024

በመላው ዓለም የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች፣ ቅዱሱ የረመዳም ጾም ወር መጠናቀቁን የሚያበስረውን የኢድ አልፈጥር በዓል ዛሬ ረቡዕ አክብረዋል።

ሆኖም የበዓሉ አከባበር እየተባባሰ በሄደው የጋዛ መጣው ቀውስ እና እስራኤል በራፋህ ከተማ ላይ ታካሂዳለች የተባለው ጥቃት ባጠላበት ሁኔታ አልፏል።

"ፍልስጥኤማውያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንን መርሳት የለብንም" ያሉት፣ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ የሚገኙት ኢማም አብዱል ራህማን ሙሳ ሰይድ፣ "ዓለም በዝምታ እያየ፣ ያለምንም ምክንያት ወረራ እና ጥቃት እየተፈፀመባቸው ነው" ብለዋል።

የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬቺፕ ታዪብይብ ኤርዶጋን ለበዓሉ ባስተላለፉት መልዕክት "በሰው ልጅ ህሊና ላይ የሚደማ ቁስል" ሲሉ ለገለፁት ጋዛ ድጋፋቸውን ገልፀዋል። በዋና ከተማዋ ኢስታንቡል “አያ ሶፊያ” መስጊድ ለፀሎት የተሰበሰቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናንም አንዳንዶቹ የፍልስጥኤምን ባንዲራ ሲይዙ፣ ሌሎች የጋዛን ነዋሪዎች የሚደግፉ መፈክሮችን አሰምተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች አጋር ተቋማት፣ ጋዛ የሚኖሩ ከአንድ ሚሊየን በላይ የሚበልጡ ሰዎች ለረሃብ አደጋ እንደተጋለጡ እና እስካሁን የሚገባው እርዳታ እጅግ አነስተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ሰዎች ከአንድ ወር የጾም እና የጥሞና ጊዜ በኃላ ስለተሰጣቸው በረከት በማሰብ በዓሉን አክብረዋል። በበዓሉ ዋዜማ ቀናት በዓለም ዙሪያ ገበያዎች በገዢዎች ተሞልተው የታዩ ሲሆን ነዋሪዎች እለቱን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማክበር ወደየትውልድ መንደሮቻቸው ተጉዘዋል።

ከዓለም ትልቁን የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ቁጥር በያዘችው ኢንዶኔዥያ ለምሳሌ ሦስት አራተኛ የሚጠጋው ህዝቧ ወደትውልድ መንደሩ 'መዲክ' ተብሎ የሚጠራውን ዓመታዊ ጉዞ ያደርጋል። በዋና ከተማዋ ጃካርታ ነዋሪ የሆነችው እና ቤተሰቦቿን ለማየት ወደ ደቡባዊው ኢንዶኔዥያ አካባቢ የተጓዘችው ሪድሆ አልፊያን "ይህ ጊዜ ከቤተሰብ ጋር የምንገናኝበት እና ለአንድ ዓመት ከቤተሰብ ርቀን ስንኖር ያጨረስነውን ባትሪ የምንሞላበት አድርገን እናየዋለን” ብላለች፡፡

በደቡብ ምስራቅ እስያ ትልቁ የሆነው እና በጃካርታ የሚገኘው ታላቁ የኢስቲክላል መስጊድም የጠዋት ጸሎት በሚያደርሱ ምዕመናን ተጥለቅልቆ ነበር። ሰባኪዎችም ላለፉት ስድስት ወራት በጋዛ በጦርነት እየተሰቃዩ ላሉ ሙስሊሞች ፀሎት እንዲያደርሱ ጠይቀዋል።

በርሊን ላይ ደግሞ ከቤኒን፣ ክጋና፣ ከሶሪያ፣ ከአፍጋኒስታን እና ከቱርክ የሆኑ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች በበዓሉን በዓለም አቀፋዊ መንፈስ አክብረው ውለዋል። በመስጊዱ ፀሎት ስታደርስ የነበረች የ45 ዓመት የአምስት ልጆች እናት "ይህ ቀን እዚህ ስላለን ነገር ሁሉ የምናመሰግንበት እና ለድሆች፣ በጦርነት ውስጥ ላሉ እና በረሃብ ለሚሰቃዩ ያለንን የምንሰጥበት ነው" ብላለች።

በማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዋር ኢብራሂም በኢድ ዋዜማ ባስተላለፉት መልዕክት አንድነት እና እርቅ እንዲኖር ጥሪ ያደረጉ ሲሆን ማንም በሃይማኖትም ሆነ በሌላ ምክንያት እንዳይገለል ጠይቀዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG